Amharic
እሳትና ጭድ
(አበበ ገላውና መለስ ዜናዊ ባንድ ክፍል)
ይነጋል በላቸው
ሰኞ፤ ግንቦት ፲ ፫ ቀን፣ ፳ ፻ ፬ ዓመተ ምህረት
ኢትዮጵያዊያን በያለንበት፤ አበበ ገላው በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ፤ መለስ ዜናዊን አንገቱን ሲያስደፋውና መግቢያ ቀዳዳ አሳጥቶ ሲያስጠብበውና ሲያስጨንቀው በቪዲዮ እያየን ነው። አበበ ደፋር፣ ትልቅና ግልፅ ነበር። መለስ ሽቁጥቁጥ፣ ትንሽና ያፈረ ነበር። አበበ ልሣኑ እስከፈቀደለት ድረስና የኢትዮጵያን ሕዝብ ድምፅ በጀርባው ጉልበቱ አድርጎና አዝሎ ነበር የመለስን ማንነት ለዓለም ያወጀው። መለስ መሬት ተሠንጥቃ ብትውጠው በወደደ ልቡ፤ የተግባሩን ቀንበር በጀርባው ተጭኖት አንገቱን ደፍቶ ነበር። አበበ ድምፅ ላጣው ቁጥር ስፍሩ ኢትዮጵያዊ፤ የገዛ ሀገሯ እሥር ቤት ለሆነባት ኢትዮጵያዊት፤ ድምፅ ነበር። መለስ የመሰሎቹን አምባገነኖች ምስል ሆኖ፤ በዓለም ፊት ዕርቃኑን ተጋለጠ። አበበ ገላዉን ምን አነሣሣው? አበበ ገላዉ ብቻውን ነው? አበበ ገላዉ ብቻውን ነበር?
ለዚህ ጥያቄ መልሱ የሚፈልቀው ራሳቸውን ከተጨቆነው ሕዝብ ጎን ካቆሙት፤ አበበ ባለበት በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ነው። አበበ ለግል ጥቅሙ ነበር ወይ ይኼን ያደረገው? የግል ቂም በቀል ነበረው ወይ? ቁጭቱን በመለስ ላይ እየተወጣ ነበር ወይ? አይደለም። አይደለም። አይደለም። ይህ ነው መልሱ። አበበ ብቻዉን አልነበረም። አበበ አዎ! አበበ ገላው መለስ ዜናዊንና በቦታው የነበሩትን የዓለም መንግሥታት መሪዎችና ሹማምንቶች ለፈተና ሲያቀርባቸው፤ ለአበበ ገላው ወይንም ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወይንም ለራሱ አጀንዳ ወይንም ለቡድን አጀንዳ ሲል አልነበረም። አበበ ኢትዮጵያዊ ነው፤ እዚያም መለስ ዜናዊን ያንቀጠቀጠው በኢትዮጵያዊነቱ ነው። አበበ በዚያ ቦታ እኔን ወክሎ ነበር። አበበ በዚያ ቦታ እርስዎን ወክሎ ነበር። እበበ እዚያ ቦታ አንቺን ወክሎ ነበር። አበበ እዚያ ቦታ አንተን ወክሎ ነበር። አበበ እዚያ ቦታ የኢትዮጵያን ሕዝብ ወክሎ ነበር። ምን አደረገ? ተግባሩ ምን ነበር? የተግባሩ ክብደትና ጥልቀት እምኑ ላይ ነው?
አበበ ገላው፤ በራሱ ሀገር በሙያው እንዳያገለግል በሩ የተዘጋበት ጋዜጠኛ፤ በአሜሪካ ይኖራል፤ ሙያዉንም ይገለገልበታል። የዓለም አቀፍ የዜና አገልግሎት ማኅበር አባል በመሆኑ ነበር ለዚህ ዝግጅት የተጋበዘው። እዚያ ቦታም የሄደው እንደ ባለ ሙያ፤ የዜና አገልግሎት ማኅበር አባልነቱ ለመሣተፍ ነበር። በሀገር አጥፊ ተግባሩ ደረቱን የሚነፋዉና ራሱን የሚያንቆለጳጵሰው መለስ ዜናዊ፤ መናገር ሲጀምር፤ አበበ ገላው ከተቀመጠበት ተንስቶ፤ ድምፁ እስከፈቀደለት ድርስ በመጮኽ፤
“መለስ ዜናዊ አምባገነን ነው!
መለስ ዜናዊ አምባገነን ነው!
እስክንድር ነጋንና የፖለቲካ እስረኞችን ሁሉ ፍታ!
ይህ የቡድን ስብስባችሁ በፀረ-ሰብዓዊነት ላይ ተሰማርቷል!
ከምግብ የበለጠ የተራብነው ነፃነትን ነው!
ከነፃነት ውጪ ምግብ ሊኖር አይችልም!
ምግብ ያለ ነፃነት ሆድ አይሞላም!
ነፃነት!
ነፃነት!
ነፃነት!”
በማለት የተሰበሰበዉን ዕድምተኛ አቅል መሣብ ብቻ አይደለም፤ ድንጋጤም ለቀቀባቸው። ይህ መልዕክት ለመለስ ዜናዊ አልነበረም። ሕዝቡ እንደማይወደው የሚያውቀው መለስ ዜናዊ፤ በሀገሩ አደባባይ እንኳን በጥይት መከላከያ መስተዋት ተደብቆ ነው ንግግር የሚያደርገው። ይህ መልዕክት ለዓለም የዜና አገልግሎት ማኅበር አባላትና፤ በነሱ አልፎ ደግሞ፤ ለዓለም ዜና ተከታታይ በሙሉ ነው። ይህ ነበር አበበ ገላው ያደረገው። ይህ ብቸኛ ተግባር፤ በዓለም የዜና አገልግሎት ማኅበር አባላት ፊት፣ በዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ መሪዎች ፊት፣ የምግብ አስተማማኝነትን ሊወያዩ በተሰበሰቡበት ወቅት፤ መለስ ዜናዊን በአደባባይ እንደወጣች አይጥ አንገቱን ያስደፋው ክንውን፤ ድፍረት፣ ቆራጠኝነትና ኃላፊነትን በትልቁ የመወጣት ተግባር ነው። የዚህ ተግባር ክብደት፣ ጥልቀት፣ እንደምታ፣ ጠቀሜታና ሕያዉነት ከዛሬ በኋላ በሚከተለው የታሪክ ሂደት የተረጎማል። ለአሁኑ ብቸኛ ሆኖ መታየቱ የጊዜ ጉዳይ ነው።
እንግዲህ ከዚህ የሚከተለው የኛ ድርሻ ነው። የአበበ ገላው ድርጊት የነጋ በጎራዴው ድርጊት ነው። የአበበ ገላው ድርጊት የሽፈራው አባ ኮስተር ድርጊት ነው። የአበበ ገላው ድርጊት የየኔሰው ገብሬ ድርጊት ነው። ይህ ድርጊት የሽብሬ ደሳለኝ ድርጊት ነው። ግለሰብ ኢትዮጵያዊያን፤ በታሪካችን ላይና ታች፤ የኢትዮጵያዊያንንና የኢትዮጵያን ፍቅር በልባቸው አዝለው፤ ጅብዱ ሠርተው ያለፉበት እኛን አሁን ያኮራናል። የአቡነ ጴጥሮስ ስም ሲነሣ አፍንጫችንን ቀና እናደርጋለን። የዘረዓይ ድረስ ስም ሲነሣ ደረታችንን አንነፋለን። የአብረሃ ደቦጭና የሞገስ አስገዶም ስም ሲነሣ ፊታችን በፈገግታ ይሞላል። እኒህ ታሪክ የሠጣቸውን የወቅቱ ጥሪ የተቀበሉና፤ የተወጡ አኩሪዎቻችን ናቸው። የፋሽስቱ የጣሊያን ወረራ ነበር የአቡነ ጴጥሮስ፣ የሽፈራው አባ ኮስትር፣ የነጋ በጎራዴው፣ የአብረሃ ደቦጭ፣ የሞገስ አስግስዶም፣ የዘረዓይ ድረስና የብዙ አርበኞቻችን ጥሪ። የዘረኛው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ነው የሽብሬ ደሳለኝ፣ የየኔሰው ገብሬና ሕይወታቸውን በዚህ ዘረኛ መንግሥት ያጡ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ጥሪ። የርስዎስ ጥሪ ምንድን ነው? ታሪክ፣ ትውልድና ሀገር ከርስዎ ባሁን ሰዓት ምን ጠይቆዎታል? አበበ ገላዉ መለስ ዜናዊን በዓለም ፊት ሲያፋጥጠው ምን ታሰበዎት? ይህ የርስዎ ስሜት ነው።
ለእኔ የተሰማኝ ቀላል አይደለም። ዘረዓይ ድረስ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከምድር አንስቶ ሲስማት ታዬኝ። ነጋ በጎራዴው ጎራዴውን መዞ የፋሽስቱን ጣሊያን ታንክ ግብግብ ሲገጥመው ታዬኝ። እኔም አለሁ ብዬ! ከነሱ ያላነሰ በመሥራት አብሬያቸው ልሠለፍ ወደድኩ። ያገሬን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጌ ልሽከም ተመኘሁ። ያገሬን ጠላቶች በጥርሴ በጣጥሼ ጎማምጄ ስጥላቸው ታዬኝ። ሀገሬን ተሸክሜ ከሌሎች ሀገሮች በፊት ሳስቀድማት ታዬኝ። እርስዎና እኔ አርበኞች ሆነን ካለችበት ማቅ ስናወጣት ታዬኝ። አንቺና እኔ አርበኞች ሆነን ካለችበት ማቅ ስናወጣት ታዬኝ። አንተና እኔ አርበኞች ሆነን ካለችበት ማቅ ስናወጣት ታዬኝ። ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ሁላችን በአንድ ድርጅት ብቻ ተሰባስበን፤ አንድ ሀገር፣ አንድ ትግል፣ አንድ ድርጅትና አንድ አጀንዳ ብለን ለሀገራችን ስንቆም ታዬኝ። ምን ይላሉ? ቅዠት ነው ይሉኛል ወይስ ይቻላል?
ይህ አጀንዳ የሕዝባችን ነፃነትና የሕዝባችን ነፃነት ብቻ ነው። ነፃነት ማለት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከዘረኛው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መገላገሏ ማለት ነው። ነፃነት ማለት ሀገራችን ኢትዮጵያ ዘረኛው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ካመጣው ከፋፋይ የፖለቲካ ፍልስፍና መላቀቋ ማለት ነው። ነፃነት ማለት ሀገራችን ኢትዮጵያ ዘረኛው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በሥራ ላይ ካዋለው ኢትዮጵያዊያንን ከፋፋይ የአስተዳደር መመሪያ መጽዳቷ ማለት ነው። ነፃነት ማለት ሀገራችን ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን መሆኗ ነው። ነፃነት ማለት ኢትዮጵያዊያን በአንድነት የራሳቸውንና የሚፈልጉትን መምረጥ የሚችሉባት ሀገር መሆኗ ነው። ነፃነት ማለት ሀገራችን ኢትዮጵያ፤ እያንዳንዱ/ዷ ኢትዮጵያዊ፤ በክልሎቿ በሙሉ፤ ያላንዳች ጥያቄ፤ በፈልገችበት/በፈለገበት መኖር፣ መሥራት፣ መበልፀግ የሚትችልባት/የሚችልባት ሀገር መሆኗ ነው። ነፃነት ማለት የሀገራችንን አንጡራ ሀብት በጋራ፤ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንባት ሀገር፤ መሆኗ ነው። ነፃነት ማለት ግለሰብ ኢትዮጵያዊያን የነፃነት ማዕከል የሆኑባት ሀገር መሆኗ ነው። እናም ግለሰብ ኢትዮጵያዊያን፤ ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተጠብቆ፤ በአንድነት፤ አንድ ሕዝብ፣ አንድ ሀገር፣ አንድ ነፃነት ብለው፤ ሀገራቸውን ከድንቁርና፣ ከበሽታ፣ ከድህነትና ከኋላቀርነት የሚላቀቁባት ሀገር መሆኗ ነው። ምን ይሉኛል? ቅዠት ነው ይሉኛል ወይስ ይቻላል? ምን ትይኛለሽ? ቅዠት ነው ትይኛለሽ ወይስ ይቻላል? ምን ትለኛለህ? ቅዠት ነው ትለኛህ ወይስ ይቻላል? በሉ ተነሱ! ሥራ ይጠብቀናል።
